Facebook o girmay reda

Powered By Blogger

Followers

Sunday, January 31, 2010

ጋሽ ገቢ ናፈቀኝ!!

በሃሳቤ አዲስ አበባ ፤ከአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በታች ወንዙን እንደተሻገሩ ባለው የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቴያን የግንብ አጥር ተደግፊ ጫማዬን እያስጠረኩ ነው። መቼም ቀኑ እሁድ ጠዋት መሆን አለበት። በሰማያዊው ሰማይ ላይ ደስ የምትል ፀሃይ ወጥታለች። ዙሪያዬን በሰፈር ልጆች ተከብቤያለሁ። በመኪና መንገዱ ላይ ጎረምሶች ኳስ ሲጫወቱ ለአላፊ አግዳሚው ቁብ አይሉም። ከፊት ለፊቴ በቀበሌው መዝናኛ ክበብ ውስጥ ያለው የታሪኩ ሥጋ ቤት መስኮቱን ለጠዋት ፀሃይ ወለል አድርጎ ከፍቷል። ትንሽ አለፍ እንዳሉ የአረቦ ሱቅ አለ። ጋሽ ገቢ የገዛውን ሲጋራ ለኩሶ ሲወጣ ይታየኛል።ትኩረት አልሰጠሁትም። አጠገቤ ካሉት ልጆች ጋር ወሪዬን እጠርቃለሁ። ያው እንደተለመደው ፥የእንግሊዝ ፕሪሚሪ ሊግ ጨዋታ፣ የቅዳሜ ጋዜጦች እትም ፣የቅዳሜ ምሽት ጀብዱ ፣የዓለም ፖለቲካ ፣የመንግስት ባለስልጣናትን እና ታዋቂ ሰዎችን ማማት………ጫዋታው ያጓጓል። ሳቅ……..…ውካታ!!

ሁሌም እሁድ ጠዋት ልማዳችን ነው። የበረሮ ቀልድ፣ የታምሩ ሳቅ፣ ‘የጓድ አብዱ’ ትንታኔ………….ሁሌም ተነፋቂ ነው። በጨዋታ መሃል በረሮ ጋሽ ገቢን ከታሪኩ ሥጋ ቤት ሥጋ ገዝቶ ደረጃውን ሲወርድ ያየዋል።

“ እንዴ……..ጋሽ ገቢ! ምንድነው ያንጠለጠልከው ? ” ይለዋል እየሳቀ። ጋሽ ገቢ የበለዘ ጥርሱን እያሳየ በጣቶቹ ከንፈሩን ፈትጎ..

“ እናታችሁን ል….። ምቀኛ ሁላ! ይህችን ቅንጥብጣቢ ይዢ ብገባ አይናችሁ ደም ለበሰ። እናቴ ….…እናንተ ጠጡ፥ እኔ ባገኘኋት እበላለሁ። ”

ሁሉም ሳቁን ለቀቀው። በህይወቴ እንደዚህ ስድብ እምጠላው የለኝም። ጋሽ ገቢ ግን ሲሳደበው ምንም ሳይመስለኝ ለምን እንደምስቅ አይገባኝም። ታዲያ እኔ ብቻ አይደለሁም ፤ሁሉም ይሄን ስድቡን ይወድለታል። ማንም እንደሚለውና እንደተስማማበት ይሄ ስድብ ጋሽ ገቢ ላይ ያምራል። በእያንዳንዱ ንግግር መጀመሪያ ይህን ስድብ እንደመቅድም ካልተጠቀመበት ንግግሩ ንግግር፣ ጨዋታው ጨዋታ አይሆንም። የሰፈር ልጆች እንደሚናገሩት፤ ይሄ ስድብ ጋሽ ገቢ ላይ ዜማ አለው። ገብስማ ፀጉሩን በጣቶቹ እየቆፈረ “ እናትህን ል…..” ብሎ ሲሳደብ፥ የሚሰማው አላፊ አግዳሚ ሁሉ “ ምን አይነት ቅሌታም ሽማግሌ ናቸው! ” ብሎት እየሳቀ ያልፋል። እድለኛ ነው……….. ማን ይቀየመዋል!!

ጋሽ ገቢ መቼ እንደተወለድ የሚያውቅ የለም። እሱ እንደሚለው አዲስ አበባ መሃንዲስ መምሪያ ያለው ጦር በደርግ ላይ አምፆ እነ ሻምበል ፍቅረስላሴ አመፁን ለማክሸፍ በሄዱበት ጊዜ ወታደር ሆኖ እዚያው መሃንዲስ ጊቢ ውስጥ ነበር።

“ ታዲያ ያኔ……አንድ ሃያ ዓመት ይሆነሃል። ” ብሎ አንዱ ሲለው፤

“ እናትን ል…..። ሰውነቴ ወፍራም ስለነበር ወታደርነት ቀጠሩኝ ፤እንጂ እድሜዬስ ገና አስራ አራት አይሞላም ነበር። ”ብሎ ይመልሳል። በረሮ በጫዋታ መሃል ሲያበሽቃው “ ንግስት ዘውዲቱ ሲወለዱ ከበስተግርጊ ኩራዝ ይዞ ቆሞ ነበር። እንግዲ ያኔ ያንድ ያአስር ዓመት ልጅ ሳይሆን አይቀርም። ” ይለዋል።

ጋሽ ገቢ በቀድሞው መንግስት የምድር ጦር ውስጥ የመገናኛ ይሆን የማመላለሻ ሹፊር ነበር። እንደማስታውሰው ማዕረግ የነበረው ሲሆን፥ በሠራዊቱ ውስጥ የ አምሳ አለቅነት ሹመት ላይ ደርሷል። ጋሽ ገቢ ይህ ስሙ እውነተኛ ስሙ አይደለም። እናት እና አባቱ ያወጡለት የመዝገብ ስሙ “ ይታገስ ”ሲሆን፥ ለምን ጋሽ ገቢ እንደተባለ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ፤ማንም ግን በትክክለኛ ስሙ ጠርቶት አያውቅም።

……………ዛሪ እዚህ ያለሁበት ቦታ ሆኜ ጋሽ ገቢ ናፈቀኝ። እኒያ በውሸት የተሞሉ ለዛ ያላቸው ጨዋታዎች፣ አጋኖ የሚያወራቸው ጀብዱዎቹ፣ ስድቡ፣ ርህራሄውና ደግነቱን..……እያስብኩ ፈገግ ለማለት እሞክራለሁ። አንዳንዴ……ይሄ ሃምሳ ዓመት በርግጥ ያለፈው ሰውዬ…….ድልደል ያለ ሰውነቱ ላይ ያለው ቦርጭ፣ ገብስማ ፀጉሩን፣ የበለዘ ጥርሶቹን፣ ሲጋራ የማይለየቸው ጣቶቹን በአይነ ህሊናዬ እየቀሰርኩ ያለፈ ታሪኮችን በእዝነ-ልቦና ለማጠንጠን እሞክራለሁ…………….።

…………………… “ ያኔ እናታችሁን ል……….” ይለናል ጋሽ ገቢ ጨዋታውን ሲጀምር…… “ አስመራ የሚገኘው የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አባል ነበርኩ። ያርፍንበት የሠራዊት ካንፕ ውስጥ የምንተኛው በቡድን-በቡድን ሆነን በተሰጠን የማርፊያ ክፍል ውስጥ ነበር። አንዴ…..ሳይታሰብ ጀነራል ቁምላቸው ሊጎበኝን መጣ። ገና ወደክፍላችን ሲገባ ሁላችንም በድንጋጤ ከአልጋችን ላይ ተስፈንጥረን በባዶ እግራችን ወለሉ ላይ በተጠንቀቅ ቆምን። የምንኖርበት ቤት ምስቅልቅሉ ወጥቶ፤ እያንዳንዱ ወታደር የከፈተው ሙዚቃ ጩኀት ክፍሉን አደንቁሮት፤ የወታደር ማደሪያ ካምፕ ሳይሆን ዳንስ ቤት መስሎ ነበር በድንገት ‘ ዘው ’ ያለው። “ ምንድነው ይህ ሁሉ ስራት አልበኝነት?..... ዳንስ ቤት ነው ወይስ የወታደር ካንፕ? ”አልን አይኖቹን አፍጥጦ። የምንለው ጠፍቶን፥የምንገባበት ቀዳዳ መፈለግ ያዝን። እሱ ሙሉ የማዕረግ ልብሱን እንደለበሰ በትረ መኮንኑን በቀኝ እጁ ጨብጦ ግራኛው እጁን እየመታ በመንጎራደደ የእያንዳንዳችንን አልጋ ይጎበኝ ጀመር። ልክ እኔ ጋር ሲደርስ እፊት ለፊቴ ቀጥ ብሎ ቆመና ለረጅም ጊዜ አፍጥጦ ይመለከተኝ ጀመር። ወዲያው ቀና ብሎ ከአልጋዬ በላይ በተዘረጋ ገመድ ላይ እንዲደርቁ ያንጠለጠልኳቸውን ካልሲዎች እየተመለከተ፥ በበትረ መኮንኑ እንዲህ ወደላይ እየነካካቸው………….. “ምንድን ነው ይሄ?........ቋንጣ ነው?? ” አለኝ። ላብ በላብ ሰውነቴ ርሶ፤ በድንጋጤ ክው ብዬ ደርቄ ቀረሁ።………….”

ሁላችንም ትረካውን እየሰማን በሳቅ ፈረስን። ይሄኔ አብሮ አደጉ እና ጓደኛው የቀድሞ ጦር ሻምበል የነበረው ታዬ እየሳቀ….. “ እንዴ ምንድን ነው የምትለው?.......ጄነራል ቁምላቸው የአየር ወለድ አዛዥ ነው። እናንተ ጋር ምን ሊያደርግ ይመጣል? ”ብሎ ያፋጥጠዋል። ጋሽ ገቢ ያው የተለመደ ስድቡን በማስቀደም “ እናትን ል…። ዝምብልህ አዳምጥ! ወሪ አታቆርፍድ። ” ብሎ ይመልስለታል።

የጋሽ ገቢ የጦር ቤት ታሪክ መዝናኛችን ነበር። በረሮ በሚስቁ አይኖቹ ጋሽ ገቢን እየተመለከተ “ እስቴ ስለሸጥከው ታንክ ንገረን። ” ይለዋል።

“ እሱ እኮ አሁን ነው።…….” ብሎ ከንፈሮቹን እንደተለመደው በሁለት ጣቶቹ አይበሉባ እየጥረገ መተረክ ይጀምራል። “………. መንጌ ጠፋ ሲባል ያ-ሁሉ ሠራዊት ልክ ለሱ የሚዋጋ ይመስል፥ ከየግንባሩ እየፈረጠጠ ወደ አዲስ አበባ ሲሸሽ ፤እኔ ያኔ መተሃራ ነበርኩ። እኔስ ማን አለኝ? ምን አደርጋለሁ? ብዬ የምነዳውን አይፋ መኪና እያብረርኩ ወደ ናዝሪት ነጎድኩ። ልክ ናዝሪት መግቢያው ላይ ስደርስ አካባቢው ትርምስ በትርምስ ሆኗል። የሚሸሸው እግረኛ ሠራዊት፣ ታንኩ፣ የተጠመዱ ከባባድ መሳሪያዎች ሁሉ እዚህ ፈሰዋል። በመንገዱ ላይ የነበረው ሙቀት ድካም ለቆብኝ ነበረና እንዲሁም ውሃ ጠምቶኝ ስለነበር፤ መኪናዬን ከመንገዱ ዳር ወጣ አድርጌ በማቆም የሚጠጣ ፍለጋ ወደ አንድ ቡና ቤት አመራሁ። በአጋጣሚ እግሪ ገና የቡና ቤቱን በር ገባ እንዳለ፤ አንድ ስሜን ታንከኛ የነበረ የማውቀው ሻምበል ባሽ ላይ አይኖቼ አረፈ። እሱም ወዲያው አይቶኝ ነበር እና “ ገቢ…..እናትህን ል…፡ በህይወት አለህ?! ……አልሞትክም! ” አለኝ። ለብዙ ዓመታት አልተያየንም ነበር እና በናፍቆት ተሳስመን ወጋችንን እንጠርቅ ጀመር። በወሪ መሃከል ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንደሚፈልግ ፤ግን ታንክ መያዙን እና የሚገዛ ቢያገኝ ለመሸጥ ወደኋላ እንደማይል ነገረኝ። እኔም ወደ ተራራው አካባቢ የማውቃቸው ገበሪዎች እንዳሉና ይገዙ እንደሆን እድላችንን እንድንሞክር ጠየኩት። ወዲያው ያዘዝኩት ቢራ ከጉሮሮዬ ሳይወርድ እያካለብኩ ይዤው ወጣሁ። ከዋናው መንገድ ተገንጥሎ ባለው ኮሮኮንች መንገድ እየነዳሁ ወደተራራው ስወጣ ከኋላዬ ታንኩን እያንደረደረ ተከተለኝ። ተራራው ጥግ ስንደርስ ሁለታችንም የምንነዳውን አቁመን፤ እኔ ከመኪናዬ በመውረድ ‘ ወደገበሪዎቹ መንደር በመግባት አነጋግሪ እስክመጣ ድረስ እዚሁ እንዲጠብቀኝ ’ ነግሪ ተለየሁት። ከሱ ተነጥዬ ወደመንደሩ ስገባ ፤ከዛፍ ስር አራት ገበሪዎች ቁጭ ብለው ሲጨዋወቱ ደረስኩ። ያው ከዚህ ቀደም በዚያ መንገድ የሚጠጣ ጠላ ፍለጋ ብዙ ግዜ ሰፈራቸው ስመላለስ ተዋውቀን ነበረና ከተቀመጡበት በመነሳት ሰላምታ አቀረቡልኝ። እኔም ወደ ዋናው ጉዳዬ ቶሎ በመግባት ፤ ለሰፈሯ ዕድገት ጥሩ ዕድል ይዤ መም ጣቴን በማውሳት የሚሸጥ ዕቃ ያለኝ በመሆኑ መንደረተኛውን በማሰባስብ እንዲገዙኝ ጠየቅኳቸው። እነሱም ወዲያው በመሰባሰብ ተከትለውኝ ታንኩ ወደቆመበት ቦታ ሄዱ።

“ እሄውላችሁ…….” አልኳቸው-ታንኩን እያሳየኋቸው “………ይህ ታንክ ነው። በሰላም ግዜ ታርሱበታላችሁ። በጦርነት ግዜ ትዋጉበታላችሁ። ዋጋው አይጎዳችሁም፤ አዋጥታችሁ አርባ ሺ ብር ክፈሉ ” ብዬ ገና ከማለቴ ከመንደረተኛው መሃል ሽምገል ያሉት ገበሪ ከማህከላቸው ወጣ ብለው

“ ልጄ…….የምትለው ዕቃ ይጠቅመናል። ግን አቅማችን አይችልም። የምትል ከሆነ እኔም ከመንደረተኛው ላስባስብ አንተም ሃያ ሺ ብር አድርግልን። ” አሉኝ። እኔም ጓደኛዬን ላናግር ብዬ ወደባሻ በማምራት ያቀረቡትን ዋጋ ነግሪው ብንስማማ የሚሻል መሆኑን አስረዳሁት። እሱም በጣም ተደስቶ ገንዘቡን ቶሎ እንድቀበል ላከኝ። ወዲያውም መንደረተኛው ገንዘቡን አዋጥቶ በሽማግሌው በኩል አስረከቡኝ። እኔም ባሻን አጠገቤ አድርጊ ወደ አዲስ አበባ ነጎድኩ። በኋላ ማሳያ መስታወት የኋሊት ወደ መንደረተኛው ስመለከት ግን ገበሪዎቹ እንደ ንብ ታንኩን ከበውት በአድናቆት ሲመለከቱት አየሁ።

የጋሽ ገቢ ታሪኮች መጨረሻ የላቸውም።ከሁሉም ታሪኩ ግን እንደዚህ ያሳቀኝ የለም። ጋሽ ገቢ እራሱ ይተርክልን።……………….

………………………………… ያው የመንግሥት ለውጥ ተደርጎ ሠራዊቱ ከተበተነ በኋላ የማደርገው ጨነቀኝ። ከየትም ከየትም ብዬ ያገኘኋትን ገንዘቦች ቀረጣጥፊ በላሁና ስታልቅ ግዜ የምገባበት ጠፋኝ። በየቦታው ስራ ፍለጋ ማመልከቻ ባስገባም ለእኔ የሚሆን ጠፋ። አደለም ሲጋራ የማጨስበት ዳቦ የምበላው መግዣ አጣሁ። ጫሞቼ አልቀው በነጠላ ጫማ ማዝገም ከጀመርኩ ወደ አንድ አመት ከስድስት ወር አለፈኝ። ይሄኔ እናቱን ል…ና ይሄ ሻምበል “ ለምን አዋቂ ቤት ሄደን አንጠይቅም ? ” አለኝ። የማደርገው ነገር ጥፍት ብሎኝ ነበርና ላለመስማማት ምርጫ አልነበረኝም። ተከትዬው ሄድኩ።ቦታው ወደ ኮተቤ አካባቢ ነበር። እቤቱ ውስጥ ገብተን፤ የኔ ተራ ደርሶ መናገር ጀመርኩ።

“ ጌታዬ ………….አይጥ ገንዘው ደጄ ላይ ቀብረው እንጀራ አልወጣልህ ብሎኛል።……በርሶ መጀን እርዱኝ!! ” ብዬ ስጠይቅ፤ ከመጋረጃው ጀርባ ያለው ጎርናና ድምፅ እንዲህ አለኝ፤

“ ያንተ እንጀራ ገና ነው ………አልበሰለም።አ…ል..በ..ሰ..ለ..ም ” ብሎ ሲል ብሽቅ አልኩ።በቆምኩበት ቦታ አይኔን ዞር ሳደርግ፤ ዕጣን የሚጨስበት ገል ምድጃ ፍሙ ተንተርክኳል። ብድግ አድርኩና በእጆቼ ይዤ መጋረጃውን በመግለጥ ወደ ውስጥ በመግባት ተመለክትኩ። አንድ ሴት ነጠላ ለብሳ ቁጭ ብላለች።

“ የዚህ ምድጃ ፍም……… የኔን እንጀራ አያበስለም? ” ብዬ ከመጠየቄ

“ አይ ውጣ ! እንግዲህ ነገርኩህ። ገና ነው።…….ውጣ! ”

ከስሯ ያለው መሶብ ላይ አይኔን ጣልኩ። ባለ መቶ-መቶ ብር ኖቶች ሞልተውታል። ምድጃውን አስቀምጬ፤ መሶቡ ላይ ያለውን ገንዘብ በማፈስ ኪሲ ከትቼ ወጣሁ።ከኋላዬ…

“አስቀምጥ…….ውጋው!.........ነገርኩህ!..........ውጋው! ” የሚል ድምጽ ተከተለኝ።

ሻንበልን ትቼ፤ገንዘቡን ይዤ ወደ ቤቴ ስነጉድ፥ ‘ ውጋው! ” የሚለው ድምጽ እረፍት ነሳኝ። “ የበላይ አለ አይደለም እንዴ! ” በማለት ቀጥታ ወደ ሚካኤል ቤተ ክርስቴያን በመሄድ ጸሎት አደርስኩና፥ ከውሰድኩት ገንዘብ ላይ ቆንጥሪ የምፅዋት ሙዳይ ላይ በማኖር መፅለዬን ቀጠልኩ።

“ እንግዴህ ሚካኤል……..እኔን የሚወጋ ከሆነ፤አንተን አልፎ ይምጣ! ” አልኩ-- በመኩራራት።

…………………………….በዛን ሰሞን የአባባ ታምራት ነገር የከተማው መወያያ በነበረ ጊዜ፤ የሰፈር ልጆች ጋር ደውዬ ስለሁኔታው ስጠይቅ፥ ከሚሄዱት ታላላቅ ሰዎች መሃከል አንዱ ጋሽ ገቢ ነው ተብሎ እንደሚታማ ነገሩኝ። በሌላ ጊዜ ለሱ ደውዬለት ስለሚታመው ነገር ባነሳበት፥ የተለመደ ስድቡን አስቀድሞ…… “ እናታቸውን ል…….።ስሜን ሲያጠፉ ነው።………ይሄ ሁሉ ገቢ ለምን አለፈለት ብለው ተቃጥለው ነው። አንጀታቸው ይቃጠል….እኔ እንደሆነ ካለአንድ መድሃኔዓለም የማውቀው የለኝም!! ” ብሎ ተገዘተ።

እንዳልኩት የጋሽ ገቢ ታሪክ መጨረሻ የለውም። አንድ ቀን የቀረውን እንመለስበት ይሆናል።

የሆኖ ሆኖ፤ እኔ ግን እግዜር ከፈቀደ በሚቀጥለው መስከረም አዲስ አበባ ለመሄድ ቀጠሮ ይዣለሁ። ያኔ በመጀመሪያ ላያቸው ከምፈልጋቸው ሰዎች መሃከል ጋሽ ገቢ አንዱ መሆን አለበት። መቼም ገና እንዳየኝ “ እናትን ል…..አንተ! ደግሞ መጣህ!? ” ብሎ በአድናቆት ሲያቅፈኝ ይታየኛል።

እግዜር ለዛ ያብቃን።

No comments:

Post a Comment

About Me